የደብረ ታቦር ዩኒቨርሲቲ የክርስትና እምነት ተከታይ ተማሪዎች እና የዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ የ2016 ዓ.ም ትንሣኤ በዓልን በጋራ አከበሩ።
የደብረ ታቦር ዩኒቨርሲቲ ክርስትና እምነት ተከታይ ተማሪወች በተማሪወች አገልግሎት ዳይሬክተር ጽ/ቤት እና በተማሪወች ህብረት አስተባባሪነት በተዘጋጀው የ2016 ዓ.ም የፋሲካ በዓል ላይ የዩኒቨርስቲው ከፍተኛ አመራሮች፣ ዲኖች፣ ዳይሬክተሮች እና ሌሎች የስራ ሀላፊወች እንዲሁም የዩኒቨርሲቲው ተማሪወችና ማህበረሰብ በተገኙበት የፋሲካ በዓልን በደመቀ ሁኔታ በጋራ አክብረዋል።
የዩኒቨርስቲው የአካዳሚክና ምርምር ምክትል ፕሬዚዳንት ዶር መንበሩ ተሾመ በፕሮግራሙ ላይ ተገኝተው በዩኒቨርሲቲው ማኔጅመንት እና በራሳቸው ስም የእንኳን አደረሳችሁ መልክት ያስተላለፉ ሲሆን የትንሳኤን በአል ከዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ ጋር በመሆን ከተማሪወቻቸው ጋር የበአሉ ተካፋይ በመሆናቸው የተሰማቸውን ደስታ በመግለጽ ለክርስትና እምነት ተከታይ ተማሪወች፣ መምህራን እና ሰራተኞች በሙሉ እንኳን አደረሳችሁ መልካም ፋሲካ በማለት መልካም ምኞታቸውን አስተላልፈዋል። ዶር መንበሩ አክለው እንደገለፁት አመታዊ በአላትን ከተማሪወቻችን ጋር ይህን በመሰለ ቤተሰባዊነት ማክበር ዩኒቨርሲቲው በልዩ ትኩረት የሚፈጽመው ተግባሩ መሆኑን ጠቅሰው ዛሬ የተዘጋጀው የትንሣኤ በዓል ዝግጅትም ተማሪወቻችን በዓልን ከቤተሰብ ጋር አብረው እንዳሳለፉ እንዲሰማቸው የሚያደርግ በመሆኑ ለአዘጋጆችና አስተባባሪወች እንዲሁም ለበዓሉ ተሳታፊወች በሙሉ ምስጋና አቅርበዋል።
የዩኒቨርሲቲው የተማሪወች ህብረት ፕሬዚዳንት ተማሪ ሀብታሙ ተማሪወችን በመወከል መልክት ያስተላለፈ ሲሆን ለክርስትና እምነት ተከታይ ተማሪወች፣ መምህራንና እና ሰራተኞች እንዲሁም ለደብረ ታቦር ከተማ እና አካባቢው ማህበረሰብ በሙሉ እንኳን ለብርሀነ ትንሣኤ ፋሲካ በዓል አደረሳችሁ በማለት መልካም ምኞቱን በመግለጽ ለተደረገው ዝግጅት ሁሉ ለዩኒቨርሲቲው ምስጋና አቅርቧል።
በበዓሉ ዝግጅት ከተማሪወች ጋር የተገኙት የዩኒቨርስቲው ከፍተኛ አመራሮች፣ እና የስራ ሀላፊወች የዘንድሮው የትንሳኤ በአል ዝግጅት በዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ ዘንድ እርስ በርስ ቤተሰባዊ ስሜትን የፈጠረ እንደነበረ በመግለጽ በዝግጅቱ ተሳታፊ በመሆናቸው መደሰታቸውን ገልፀዋል።
ደብረ ታቦር ዩኒቨርሲቲ ለመላ የክርስትና ዕምነት ተከታይ ኢትዮጵያውያን መልካም የትንሳኤ በዓል ይመኛል።