
“የደብረ ታቦር ህዝብ ደጀን በመሆን ትክክለኛውን ኢትዮጵያዊ ማንነታችንን ስላሳዬ አመሰግናለሁ” ዶ/ር አነጋግረኝ ጋሻው-የደብረታቦር ዩኒቨርስቲ ፕሬዝዳንት

ነኅሴ 07/2015 ዓ.ም (የትምህርት ሚኒስቴር) የ2015 ዓ.ም 12ኛ ክፍል ፈተና ከመላው ኢትዮጵያ ወደ ደብረታቦር ዩኒቨርስቲ የተመደቡ ሁሉ በሰላም ወደመጡበት ተሸኚተዋል።
የደብረታቦር ዩኒቨርስቲ ፕሬዝዳንት ዶ/ር አነጋግረኝ ጋሻው ቦታው ግጭት የተቀሰቀሰበት እንደመሆኑ ህዝቡ ደጀን በመሆን ትክክለኛውን ኢትዮጵያዊ ፍቅር እና ማንነታችንን ባያሳይ ኖሮ በታሪክ ተወቃሽ የምንሆንበት መጥፎ አጋጣሚ ሊፈጠር ይችል ነበር ብለዋል።
የመጨራሻዎቹ ሶስት ቀናት ግጭቱ እየተካሄደ ነው ፈተና ስንፈትን የነበረው ያሉት የዩኒቨርስቲው ፕሬዝዳንት ዩኒቨርስቲዉ የህዝብ ነው፤ እገዛውን የጠየቅነውም ህዝቡን ነዉ ፤ በመሆኑም ህዝቡ ከጎናችን ሆኖ በጊዜው በዩኒቨርስቲው የነበሩ 6,743 ተማሪዎች፣ 300 የፈተና አስታባባሪዎችና 88 የፌዴራል ፖሊስ አባላት ሁሉም በሰላም ወደመጡበት ተመልሰዋል ብለዋል።
ተማሪዎችንም ሆነ የጸጥታ አካላትን በሰላም ስንሸኝ የሀይማኖት አባቶችና የሀገር ሽማግሌዎች ከፊትና ከኋላ በመሆን የኢትዮጵያ ባንዲራ ይዘው መንገድ በማስከፈት፣ በአባታዊ ምክር እና በፍጹም ኢትዮጵያዊ ጨዋነት ወደየመጡበት እንድንሸኝ አድርገዋልና ሊመሰገኑ ይገባል ብለዋል።
የደብረ ታቦር እና የደቡብ ጎንደር ዞን ማህበረሰብ የጊዜውን ድንቅ ታሪክ በኢትዮጵያዊነት ደማቅ ቀለም በክብር ጽፋችኋልና ልትኮሩ ይገባችኋል በማለት አድናቆታቸውን ገልፀው የኢትዮጵያ ሰላም ለማረጋገጥ ቆሞ ከማየት የበኩልን ድርሻ በግልም በቡድንም መወጣት እንድንችል አስተማሪ ይሆናል ብለው እንደሚያምኑም ጨምረው ገልፀዋል።