የደብረታቦር ዩኒቨርሲቲ የጋፋት ህዋ ምህንድስና ልማት ማእከል በአቪየሽን ኢኖቬሽን ኤክስፖ 2016 ባቀረበው የቴክኖሎጂ ፈጠራ ስራ 2ኛ ደረጃ አሸናፊ ሆነ።
የአቬየሽን ኢኖቬሽን ኤክስፖ “ፈጠራ ለኢኖቬሽን ልህቀት” በሚል መሪ ቃል የኢትዮጵያ ሲቪል አቬየሽን ከትራንስፖርትና ሎጀስቲክስ ሚኒስትር ጋር በጋራ አዘጋጅነት ከታህሳስ 1 እስከ ታህሳስ 6 2016 ዓ.ም. በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ በተካሄደው የአቪየሽን ኤክስፖ ላይ በመስኩ የተለያዩ የፈጠራ ስራቸውን ያቀረቡ በርካታ ተቋማት የተሳተፉ ሲሆን የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትም ይገኙበታል። ለአምስት ቀናት በሳይንስ ሙዚየም በተካሄደው በዚህ ታላቅ ኤክስፖ ላይ በደብረ ታቦር ዩኒቨርሲቲ የጋፋት ህዋ ምህንድስና ልማት ማእከል የተሰራው ሮኬት ለእይታ የቀረበ ሲሆን በአቪየሽን ኢኖቬሽን ኤክስፖ 2016 የ2ኛ ደረጃን በማግኘት ተሸላሚ ሆኗል። እስከ 20 ሺህ ጫማ ከፍታ መወንጨፍ እንደሚችል በሙከራ የተረጋገጠው ይህ ሮኬት በዩኒቨርሲቲው መምህራንና ተማሪወች የተሰራ የምርምር ውጤት ነው። በኤክስፖው ላይ በዩኒቨርሲቲው ተማሪወች የተሰሩ የድሮን እና የራዳር የፈጠራ ስራወች የቀረቡ ሲሆን በጎብኝወች እና ተሳታፊወች ከፍተኛ አድናቆት ተችሯቸዋል።
የደብረ ታቦር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶር አነጋግረኝ ጋሻው እና የኢትዮጵያ ሲቪል አቪየሽን ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ክቡር አቶ ጌታቸው መንግስቴ በኤክስፖው የማጠናቀቂያ ቀን ላይ በሳይንስ ሙዚየም በመገኘት 2ኛ ደረጃን በማግኘት አሸናፊ የሆነውን የደብረ ታቦር ዩኒቨርሲቲ የጋፋት ህዋ ምህንድስና ልማት ማእከል ቡድን ከፍተኛ አድናቆት እና ምስጋና በማቅረብ አበረታተዋቸዋል።
በደብረታቦር ዩንቨርስቲ የጋፋት ህዋ ምህንድስና ልማት ማዕከል የተሠራው “አጼ ቴዎድሮስ 2015” ተብሎ የተሰየመው ሮኬት ከሀያ ሺ ጫማ ከፍታ በላይ የተሳካ የማስወንጨፍ ሙከራውን ሚያዚያ 28/2015 በፋርጣ ወረዳ መደብ ጉብዳ ቀበሌ ጥሪ የተደረገላቸው የክብር እንግዶች ፣የሀገር ሽማግሌዎች የዩኒቨርሲቲው ማኔጅመንት ፣ዲኖች ፣ዳይሬክተሮች እና ተማሪዎች በተገኙበት ማድረጉ ይታወሳል።