የኢትዮጵያ ቤተመዛግብትና ቤተመጻሕፍት አገልግሎት ሕዳር 13/2016 ዓ.ም ከደብረ ታቦር ዩኒቨርሲቲ ጋር ዘላቂነት ያለው የጋራ የመግባቢያ ሠነድ ተፈራረመ፡፡
የተፈረመው መግባቢያ ሠነድ ዩኒቨርሲቲውንና ተቋሙን ከማስተሳሰር ባለፈ ሁለቱም ተቋማቶች ለሀገር የሚጠቅሙና ለመጪው ትውልድ የሚጠቅሙ ስራዎችን በዘላቂነት የሚሰሩ እንደሆኑ ሲጠቆም ነገር ግን ይኸው ተሞክሮ በሁለቱ ተቋማት ብቻ ሳይወሰንና ታጥሮ ሳይቀር ለጋራ የሀገር እድገት በትጋት መስራት እንደሚጠበቅና ሌሎች በዘርፉ የሚሰሩ ተቋማትንም በመጋበዝ ለለውጥ መሰራት እንደሚገባ ተጠቁሟል፡፡
የመግባቢያ ሠነዱን በማስመልከት የኢትዮጵያ ቤተመዛግብትና ቤተመጻሕፍት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር አቶ ይኩኖአምላክ መዝገቡ እና የደብረ ታቦር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዘዳንት ዶ/ር አነጋግረኝ ጋሻው ሃሳብ ሲሰጡ የመግባቢያ ሠነድ ሲፈረም ዝም ብሎ ተፈራርሞ ለማስቀመጥ እንዳልሆነ ተናግረው በመግባቢያ ሠነዱ ላይ ሠፍረው ዛሬ የተፈረሙት ሃሳቦች የአንድ ሰሞን ስራ ብቻ ሆነው እንደማይቀሩና ቀጣይነት ያላቸው እንደሚሆኑም ጠቁመው የመግባቢ ሠነዱን መፈራረም ያስፈለገበትንም ምክንያት ሲገልጹ ሥራው ሲሰራ ሁሉም ኃላፊነት ተሰምቶት የሚሰራው ለማድረግ እንደሆነም ተናግረዋል፡፡
ዶ/ር አነጋግረኝም ደብረ ታቦር ዩኒቨርሲቲ አዲስ ቢሆንም እጅግ በጣም በቆየ ባህልና ታሪክ ባለው ማህበረሰብ ብዙ የታሪክ ክስተቶች የማህበራዊ፣የኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ክስተቶች በተደረጉበት አካባቢ የተመሰረተ ተቋም እንደመሆኑ መጠን ወደኃላ ያሉ ነገሮቻችን የበለጠ እንዲገሰግሱ የሚያደርግ ተቋም እንደሆነም ጠቁመው ከመርሁ ጀምሮም ያለፈውን መልክአም ጅምር ለማስቀጠል እንደሚሰራ እና እንደ መርህ የሚከተለው የአጼ ቴዎድሮስን የእውቀትና የቴክኖሎጂ ጥያቄ የመመለሥ ታሪካዊ ኃላፊነት አለብን በማለት መሪ ቃል በማድረግ እየሰራ የሚገኝ ተቋም መሆኑን ጠቁመው ይህን ማለት ምን ማለት እንደሆነ ሲገልጹ እንደ ኢትዮጵያ ትንሽም ብትሆን በምንም መንገድ ይሁን የተገኘችውን ቴክኖሎጂ ለሀገር ጥቅም ለማዋል የተደረገውን ሙከራ የአሁኑ ዘመንም ያንን ዕውቀት ፍለጋ መቀጠል አለበት ብሎ የተነሳ ተቋም እንደሆነም ጠቁመው በዚህ ታሪክ ውስጥ ሲገኝ አዲስ ብንሆንም የዘመናዊ ትምህርት ይዘን የመጣን ተቋም በመሆናችን ነገር ግን እጅግ ጥንታዊና ታሪካዊ በሆኑ አካባቢ የተመሰረትን እንደመሆናችን አሁን ከዚህ ትልቅ ተቋም ጋር የሚደረገው ስምምነትና ስራዎች በጣም ጠቃሚ እንደሆነም ተናግረው ተቋሙ ከዩኒቨርሲቲው ጋር በጋራ መስራት ከጀመረበት ከ2013 ዓ.ም ጀምሮ በርካታ ስራዎችን በመስራት ደስተኞች እንደሆኑና በሰራችኃቸው ስራዎችም እናንተ ኩራት ቢሰማችሁም እንደተቋም ብሔራዊ ግዴታችሁን እየተወጣችሁ እኛንም የበለጠ እየቀሰቀሳችሁን በመሆኑ እናመሰግናችኃለን ብለዋል፡፡
በመጨረሻም የመግባቢያ ሠነዱን የኢትዮጵያ ቤተመዛግብትና ቤተመጻሕፍት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር አቶ ይኩኖአምላክ መዝገቡ እና የደብረ ታቦር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዘዳንት ዶ/ር አነጋግረኝ ጋሻው ተፈራርመው ዝግጅቱ ተጠናቋል፡፡