የደብረ ታቦር ዩኒቨርስቲ የሳይንስ፣ቴክኖሎጂ፣ምህንድስና እና ሂሳብ ማዕከል (DTU-STEM Center) ከ STEM Power.org ከተባለ ዓለም አቀፍ ድርጅት ጋር በመተባበር “Kids’ Program” የተሰኘ አዲስ ፕሮግራም መስጠት ጀመረ።
“Kids’ Program” ማለት ለመጀመሪያ ደረጃ ተማሪዎች መሰረታዊ የሆነ ስለ ሳይንስ፣ቴክኖሎጂ፣ምህንድስና እና ሂሳብ ትምህርቶች በተግባር ተኮር የማስተማር ስነ ዘዴ፣አቅማቸውን በሚመጥን መልኩ የሚሰጥ ስልጠና ነው። ይህ ፕሮግራም ለህጻናት በለጋ እድሚያቸው ለሳይንስ፣ ቴክኖሎጂ፣ ምህንድስና እና ሂሳብ ትምህርቶች በቂ ግንዛቤ ይዘው እንዲያድጉ ከማድረጉ በተጨማሪ የወደፊት ህልማቸውን እና ተሰጦቸውን እንዲያዳብሩ ያግዛቸዋል። ስልጠናው በመሰረታዊ የኤሌክትሮኒክስ እና የኮምፒውተር ትምህርቶች ያተኮረ ሲሆን በደብረ ታቦር ከተማ አስተዳደር ትምህርት መምሪያ ስር ካሉ 10 የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ለተመረጡ ተማሪዎች እየተሰጠ እንደሚገኝ ተገልጿል።
የምርምርና ማህበረሰብ አገለግሎት ምክትል ፕሬዚዳንት ዶክተር መንበሩ ተሾመ እንደተናገሩት፣ህጻናት የነገ ሀገር ተረካቢ በመሆናቸው አሁን ላይ ልዩ ትኩረት ተሰጥቷቸው የነገዋን ኢትዮጵያ አሁን ላይ መገንባት እንደሚገባ ገልፀው የፕሮግራሙ ተከታታይ ተማሪዎችም ይህንን እድል በአግባቡ መጠቀም እንደሚገባቸው አሳስበዋል።
የዩኒቨርስቲው ኢንዳስትሪ ትስስርና ቴክኖሎጅ ሽግግር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር መ/ር ዮናስ ጥበቡ በበኩላቸው በማዕከሉ ውስጥ እየተሰጡ ያሉ ትምህርቶች የተግባር ትምህርት በመሆናቸው፣ ተማሪዎቹ በአካባቢያቸው ያሉ ችግሮችን በመለየት ለመፍታት መሞከር እንዳለባቸው ገልጸዋል።
ሰልጠናውን በመስጠት ላይ የሚገኙት መምህር አበበ ክንዴ እና መምህር በእውቀቱ ጌቴ ስልጠናው ሙሉ በሙሉ ተግባር ተኮር ስለሆነ ህጻናቱ በጽንሰ ሃሳብ ደረጃ ያላችዉን ግንዛቤ የበለጠ ለመረዳት እንደሚጠቅማችው ገልጸዋል።
የደብረ ታቦር ዩኒቨርስቲ የሳ/ቴ/ም/ሂ ማዕከል (DTU-STEM Center) ከ STEMPower.org ጋር በመተባበር በበጋ የተግባር ት/ት አና የፈጠራ ስራ ተመሪዎችን ማሰልጠኑ የሚታወስ ነው ።