በደብረ ታቦር ዩኒቨርሲቲ ለተመደቡት የ12ኛ ክፍል ፈተና አስተባባሪዎችና ፈታኞች የጉብኝትና መስተንግዶ መርሃ ግብር ተደረገ።
ዛሬ ሐምሌ 23/2015 ዓ.ም በደብረ ታቦር ዩኒቨርሲቲ የ12ኛ ክፍል ብሄራዊ ፈተናን ለማስፈፀም ለተመደቡ አስተባባሪዎች እና ፈታኞች ዩኒቨርስቲው ከደቡብ ጎንደር ዞን አስተዳደር፣ ደብረ ታቦር ከተማ አስተዳደር የትምህርት መምሪያ እና የቱሪዝም መመሪያ ጋር በመተባበር ፕሮግራሙን ያዘጋጀ ሲሆን በዛሬው ውሎ ከቱሪስት መስህቦች መካከል አንዱ የሆነውን የውቅሮ መድሃኒያለም ቤተ ክርስቲያንን ጉብኝት ተካሂዷል።
ጉብኝቱን የመሩት የደብረ ታቦር ዩኒቨርሲቲ የአለቃ ገብረሃና ባህል ጥናት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር እና የታሪክ መምህሩ መሰረት ወርቁ እንደተናገሩት ደቡብ ጎንደር ዞን በርካታ የቱሪስት መዳረሻ ቦታዎች ያሉት ሲሆን ከነዚህም በጉና በጌምድር ወረዳ የሚገኘው የውቅሮ መድሃኒያለም ቤተ ክርስቲያን መሆኑን ገልፀው በቅዱስ ንጉስ ላሊበላ ዘመን እንደተጀመረ የሚነገርና በኋላም በ14ኛው ክፍለ ዘመን በአቡነ ተክለ ፀዴቅ እንተጠናቀቀ የሚነገር በአንድ ግዙፍ ሰንሰለታማ ድንጋይ ተፈልፋሎ የተሰራ መሆኑን አብራርተው በውስጡ ቅድስት፣ቅኔ ማህሌት፣የተለያዩ ዋሻዎች ፣የቅዱሳን የቀብር ቦታዎች የሚገኙበት ታሪካዊና ጥንታዊ ቦታ መሆኑን ለጎብኝዎች ሰፊ ገለፃ አድርገዋል።
ዳይሬክተሩ አክለውም በዞኑ የሚገኙ የቱሪዝም ቦታዎቹን ለቱሪስት ምቹ በማድረግ በኩል በተለይም ዩኒቨርስቲው፣ ከክልል እስከ ወረዳ ያሉ ባለ ድርሻ አካላት በጋራ መስራት እንደሚገባ አመላክተዋል ።
በጉብኝት መርሃ ግብሩ የተሳተፉ አስተባባሪዎች እና ፈታኝ መምህራን ባደረጉት ጉብኝት እጅግ መደሰታቸውን ገልፀው በጉብኝቱ ወቅት የጉና በጌምድር ወረዳ አስተዳደር እና ህብረተሰብ ለእንግዶቹ ላደረጉላቸው አቀባበል እና ባህላዊ መስተንገግዶ (ድንች በተልባ) መደሰታቸውን በመግለጽ አመስግነዋል።
ከጉብኝት መልስ በደብረ ታቦር ከተማ በቀጠለው ፕሮግራም የሀገር ሽማግሌዎች እና የዩኒቨርስቲው ማኔጅመንት በተገኙበት የመስተንግዶ እና የመዝናኛ ዝግጅት ተደርጓል።
የዩኒቨርስቲው ፕሬዚዳንት ዶክተር አነጋግረኝ ጋሻው በፕሮግራሙ ተገኝተው እንደተናገሩት ከመላው ኢትዮጵያ የብሄራዊ ፈተናን ለማስፈፀም የተመደቡ ፈታኞች እና አስተባባሪወች በተዘጋጀው የደብረ ታቦርን እና ደቡብ ጎንደር አካባቢ ትውውቅ እና ጉብኝት የአካባቢውን ህብረተሰብ ባህልና ታሪክ ለማወቅ እድል እንደፈጠረላችሁ ተስፋ አደርጋለሁ በማለት ንግግራቸውን የጀመሩ ሲሆን በመጀመሪያው ዙር የፈተና መርሃ ግብር ያለምንም ችግር በስኬት እንዲጠናቀቅ የፈተና ሀላፊዎች፣ፈታኞች፣ የዩኒቨርሲቲው ማኔጅመንት እና የፈተና ግብረ ሀይል አባላት ከከተማው ማህበረሰብ፣ የደብረ ታቦር ከተማ አስተዳደር እና የደቡብ ጎንደር አስተዳደር ጋር በጋራ እና በቅንጅት በመስራት ሁሉም አካላት ፈተናው በሰላም እንዲጠናቀቅ ላደረጉት አስተዋጽኦ ከፍተኛ ምስጋና አቅርበው በሁለተኛው ዙር የተፈጥሮ ሳይንስ ተማሪወች ፈተናም በቅንጅት እና በትብብር አጠናክረን እንቀጥላለን ብለዋል።
የሀገር ሽማግሌ ተወካዮች በበኩላቸው መምህራን በመጀመሪያው ዙር የፈተና ሂደት በሰላም መጠናቀቅ ያደረጉትን አስተዋፅኦ አመስግነው የፈተና አስፈፃሚዎች፣የከተማው ነዋሪዎች እና የዩኒቨርስቲው ማህበረሰብ ፈተናው ያለምንም የፀጥታ ችግር እንዲጠናቀቅ ላደረጉት ተሳትፎ በአካባቢው ማህበረሰብ ስም አመስግነዋል።
ታዋቂው የጉና ባንድ በፕሮግራሙ ወቅት ባህላዊ ጥዑመ ዜማወችን ለእንግዶቹ አቀርቧል።
በመጨረሻም የፈተና ፈፃሚዎች እና አስተባባሪወች በተደረገላቸው አቀባበልና መስተንግዶ መደሰታቸውን ገልፀው ለዩኒቨርሲቲው እና ለአካባቢው ማህበረሰብ በሙሉ ምስጋና አቅርበዋል።