በሁለተኛ ዙር የተፈጥሮ ሳይንስ የ12ኛ ክፍል ተፈታኝ ተማሪዎች በፈተና አሰጣጥ ሂደት ዙሪያ ገለጻ (Orientation) ተደረገላቸው።
ደብረ ታቦር ዩኒቨርሲቲ ሐምሌ 24 /2015 ዓ.ም በሁለተኛ ዙር የተፈጥሮ ሳይንስ የ12ኛ ክፍል ተፈታኝ ተማሪዎች በፈተና አሰጣጥ ሂደት እና ፈተናውን በስኬት ለማጠናቀቅ የሚያግዙ ሁኔታዎች ዙሪያ የትምህርት ሚኒስቴርና የፈተናወች ድርጅት የፈተና አስፈፃሚዎች፣ የዩኒቨርስቲው አመራሮች፣ የደብረ ታቦር ከተማ አስተዳደር ትምህርት መምሪያ ሃላፊ እና የደብረ ታቦር ከተማ ሀገር ሽማግሌዎች ተወካይ በተገኙበት ገለጻ ተደርጓል።
ዩኒቨርሲቲው ተማሪዎችን ለመቀበል ካደረገው የመጨረሻው ቅድመ ዝግጅት ስራ ለተማሪዎች ገለፃ (Orientation) ማድረግ ሲሆን በዚህም በተማሪዎች ምግብ ቤትና መኝታ ቤት አጠቃም፣በግቢ ቆይታቸው ሊፈፅሟቸው የሚገቡ መብትና ግዴታዎች፣ በፈተና ወቅት የተከለከሉ ተግባራት በተመለከተ፣የዩኒቨርሲው አመራሮች እና የስራ ሃላፊዎች በየዘርፍ ለተማሪወች ጠቃሚ መረጃወችን እና መመሪያዎች አስረድተዋቸዋል።
የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ዶክተር አነጋግረኝ ጋሻው በእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክታቸው የዛሬው መድረክ መመሪያዎችንና ደንቦችን ባለማወቅ ምክንያት ሊፈጠሩ የሚችሉ ችግሮች እንዳይኖሩ ለማድረግ እና ተማሪዎች የመጡበትን ዋና አላማ እንዲወጡ ለማድረግ የተዘጋጀ የመጨረሻው የቅድመ ዝግጅት ስራችን ነው ብለዋል።
ፕሬዚዳንቱ አክለውም ተፈታኝ ተማሪዎች ዩኒቨርስቲውን እንዲላመዱት በማድረግ ከቤተሰቦቻቸው በመለየታቸው የብቸኝነት እና የመደናገጥ ስሜት እንዳይሰማቸው በማድረግ ተቋሙን እንደቤታቸው እንዲቆጥሩት ለማስቻል የተዘጋጀ መድረክ መሆኑን ገልፀው ተፈታኝ ተማሪዎች ቆይታቸው የተሳካ እንዲሆን የሚጠቅሙ መልዕክቶችን በመግለፅ ለተማሪዎች ጥሩ የፈተና ጊዜ እንዲሆንላቸው ተመኝተዋል።
ተማሪዎቹ ፈተናውን ተረጋግተው እንዲፈተኑም የተፈታኝ ተማሪዎች ወላጆችን በመወከል አቶ በፍርዱ ወጨፎ ሥነ ልቦናዊ ዝግጅትን የሚያጠናክሩ አባታዊ ምክሮችን አስተላልፈዋል።
የብሄራዊ ፈተና አስፈፃሚወች እና አስተባባሪዎች የፈተና ቅድመ ዝግጅት፣ የተማሪዎች የስነ ልቦና ዝግጅት፣በፈተና ሰዓት ያሉ መብትና ግዴታዎች፣ የመልስ መስጫ ወረቀት አጠቋቆር እና ሌሎች ተያያዥ የፈተና መመሪያና ደንቦችን በተመለከተ ሰፊ ገለፃና ማብራሪያ ሰጥተዋል።
ዩኒቨርስቲው ባለፉት ሁለት የቅበላ ቀኖች ወንድ 3ሺ121፣ ሴት 3ሺ 508 በድምሩ 6ሺ 629 የተፈጥሮ ሳይንስ ተማሪዎችን ተቀብሎ ለማስፈተን ዝግጅቱን አጠናቋል።
የሁለተኛው ዙር የተፈጥሮ ሳይንስ ፈተና ከሃምሌ 25 እስከ 28/2015 ዓ.ም ድረስ እንደሚሰጥ ይታወቃል፡፡
# መልካም ፈተና!!
#ደብረ ታቦር ዩኒቨርስቲ