
የደብረ ታቦር ዩኒቨርስቲ በ160 ሚሊዮን ብር ወጭ ያሰራውን የንፁህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክት ርክክብ ዛሬ ህዳር 06፣2017 ዓ.ም በደማቅ ስነ-ስርዓት አከናወነ ፡፡
በርክክብ መርሃግብሩ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የደብረ ታቦር ዩኒቨርስቲ የአካዳሚክ ምርምር ጉዳዩች ምክትል ፕሬዚዳንት የሆኑት ዶ/ር መንበሩ ተሾመ እንደገለጹት ውሃው በሰከንድ 28 ሊትር የሚያመነጭ ቢሆንም አሁን ላይ በሰከንድ 23 ሊትር ውሃ እያመነጨ መሆኑን ገልጸው ይሁን እንጅ የከርሰ ምድር ውሃ አላቂ መሆኑን ታሳቢ በማድረግ ለወደፊት ሊያጋጥሙ የሚችሉ ችግሮችን በመለየት የመፍትሄ ሀሳብ ሊያመነጩ የሚችሉ ጥናትና ምርምሮች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ገልጸዋል ።
የደብረ ታቦር ከተማ አስተዳደር ከንቲባና የውሃ ቦርዱ ሰብሳቢ የሆኑት አቶ ደሴ መኮንን በርክክብ ስነ-ስርአቱ ላይ ባደረጉት ንግግር ፤ የከተማው ህዝብ የመጠጥ ውሃ አቅርቦት አሳሳቢና የከፋ ችግር ያለበት መሆኑን የደብረ ታቦር ዩኒቨርሲቲ በመረዳት ይህነን የንጹህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክት ከጫፍ ማድረሱ በማህበረሰቡ ላይ ያለውን የውሃ ችግር የሚያቃልል መሆኑን በማውሳት ምስጋናቸውን ገልጸዋል፡፡
የደቡብ ጎንደር ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ጥላሁን ደጀኔ በበኩላቸው ባደረጉት ንግግር የደብረ ታቦር ዩኒቨርሲቲ የማይቻለውን በማለምና ያለመውን በማሳካት መጀመርን ብቻ ሳይሆን መጨረስን ባህል ማድረጉን ጠቅሰው ከመማር ማስተማሩ ጎን ለጎን ከዚህ ቀደም በተለያዩ ዘርፎች በርካታ የማህበረሰብ አገልግሎት ስራዎችን መስራቱን እና አሁን ደግሞ ለሰው ልጅ ህይዎት የሆነውን ውሃ ተደራሽ ለማድረግ የሰራው ስራ ልዩ ትርጉም የሚሰጥ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በመርሐግብሩ ጠቅለል ያለ ሪፖርት ያቀረቡት የአስተዳደርና ልማት ምክትል ፕሬዚዳንት የሆኑት ዶ/ር ፍሬህይወት እንዳለ ተቋሙ ከምስረታው ጀምሮ የአካባቢውን ችግር ለመቅረፍ የሚያስችሉ በርካታ ተግባራትን ማከናወኑን አውስተው ይኸኛው ታሪካዊ ስጦታ ለታሪካዊቷ ከተማችን መሆኑ ልዩ እንደሚያደርገው የገለጹ ሲሆን አያይዘውም ተቋሙ በቀጣይም ከአካባቢው ማህበረሰብ ጋር እጣትና ቀለበት በመሆን በመሠረታዊነት የማህበረሰባችንን ህይወት የሚለውጡ ተግባራትን በብርታት እናከናውናለን ሲሉ ገልጸዋል ።
በመርሀግብሩ ላይ የደቡብ ጎንደር ዞን እና ወረዳ አመራሮች፤ የእምነት አባቶች ፤ የውሃ ፎረም አባለት እና የሀገር ሽማግሌዎች የተገኙ ሲሆን በሰጡት አስተያየትም ዩኒቨርስቲው የአመታት የውሃ ጥም አንግልተቻን ይቀረፍ ዘንድ ላበረከተው የላቀ አስተዋጽኦ ምስገናቸውን ገልጸዋል ፡፡













