በደብረ ታቦር ዩኒቨርስቲ በተለያዩ የትምህርት መስኮች ትምህርታቸውን ሲከታተሉ የነበሩ ተማሪዎች በዛሬው ዕለት ተመረቁ፡፡
- Categories አማርኛ ዜና
- Date October 5, 2024
በደብረ ታቦር ዩኒቨርሲቲ በተለያዩ የትምህርት መስኮች ትምህርታቸውን ሲከታተሉ የነበሩ 733 ተማሪዎች የዩኒቨርሲቲው ሴኔት መስከረም 23/2017 ዓ.ም ምረቃቸውን ባጸደቀው መሰረት በዛሬው ዕለት የምረቃ ስነ-ስርዓቱ የተከናወነ ሲሆን ከነዚህ መካከል 55ቱ የሕክምና ተማሪዎች (Doctor of Medicine) ናቸው፡፡ የደብረ ታቦር ዩኒቨርሲቲ የአካ/ምር/ጉዳዮች ምክትል ፕሬዚዳንት ዶ/ር መንበሩ ተሾመ በመክፈቻ ንግግራቸው እንደገለጹት፣ ተመራቂ ተማሪዎችን ከረጅም ጊዜ አድካሚ የትምህርት ጉዞ በኋላ በህይወታችሁ የመጀመሪያ ፈር ቀዳጅ ለሆነው የምረቃ በዓል እንኳን በሰላም አደረሳችሁ፤ያሉ ሲሆን የደብረ ታቦር ዩኒቨርስቲ የጤና ሳይንስ ኮሌጁ ከተመሠረተበት ጊዜ ጀምሮ በኢትዮጵያ በዓይነቱ የመጀመሪያ የሆነውን Hybrid Innovative Curriculum (ቅይጥ) ፈጠራ-አከል ትምህርት) በመተግበር በጤና ሳይንስ ትምህርት ፋና ወጌ ሆኗል። በዚህ በአይነቱ ልዩና ውጤታማ የማስተማር ስነ-ዘዴ 8 የመጀመሪያ ዲግሪና 5 የድህረ ምረቃ መርሐ ግብሮች ተከፍተው ተማሪዎችን በማስተማር ላይ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡ የማስተማር ስነዘዴው ተማሪዎች በጤና ዘርፍ ላይ ተጨባጭ ተጽእኖ ለመፍጠር እውቀትን ብቻ ሳይሆን ተግባራዊ ክህሎቶችን እና በራስ መተማመንን እንዲያዳብሩ ያስቻለ መሆኑን እና በኢትዮጵያ የጤና ባለሙያዎች ትምህርት ላይ የላቀ ሚና መጫወቱን በርካቶች ማረጋገጣቸውን ገልጸዋል። ዶ/ር መንበሩ ተሾመ ለተማሪዎቹ ባስተላለፉት ቁልፍ መልዕክት አሁን የሰጠናችሁ ዲግሪ ሁለት ነገሮችን አጣምሮ የያዘ ነው፡-1ኛው፡- የህይወት መንገድ መክፈቻ ቁልፍ በመሆኑ የሚጋጥማችሁን መልካም አጋጣሚ በአግባቡ ለመጠቀም እንዲሁም አስቸጋሪ ሁኔታዎች ሲገጥሙ መፍቻ መሳሪያ እንዲሆናችሁ፣ 2ኛው፡-ሃገራችን ከድህነት አረንቋ ለመውጣት በምታደርገው ትግል ወሳኝ ሚና የሚጫወተውን ዕውቀት የጨበጣችሁ በመሆኑ፣ እነዚህን ሁሉት ነገሮች በማጣመር የሃገራችንን የእድገት ጉዞ ለማፋጠን የበኩላችሁን አስተዋጽኦ እንድታበረክቱ የዩኒቨርሲቲያችን የአደራ ማህተም ያረፈበት ዲግሪ መሆኑን እየገለጽኩ መልካሙን ሁሉ እንዲገጥማችሁ በመላው የዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ ስም እመኛለሁ ሲሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡ በዕለቱ ከተመረቁ ተማሪዎች መካከል ከጤና ሳይንስ ኮሌጅ Doctor of Medicine 55 በሌሎች የጤናሳይንስ የትምህርት መስኮች የሁለተኛ ዲግያቸውን የተከታተሉ (MSc) 27 በልዩ ልዩ የትምህርት መስኮች የሁለተኛ ዲግያቸውን የተከታተሉ (MSc) 2 PGDT 649 በአጠቃላይ 733 ተማሪዎች መመረቃቸውን የደብረ ታቦር ዩኒቨርስቲ የሬጅስትራር እና አልሙናይ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር የሆኑት አቶ አበባው ታደሰ በምርቃ ስነ-ስርዓቱ ላይ ገልጸዋል፡፡ የደብረ ታቦር ዩንቨርሲቲ የጤና ሳይንስ ኮሌጅ ተማሪዎች በጤና ሚኒስቴር የሚሰጠውን የሙያ ፈቃድ ፈተና (Licensure Exam) ለተከታታይ አመታት አመርቂ ውጤት በማስመዝገብ ከሀገሪቱ ግንባር ቀደም መሆኑ የሚታወስ ሲሆን በመጨረሻም በትምህርታቸው የላቀ ውጤት ላስመዘገቡ ተማሪዎች የሜዳሊያ ፤ የዋንጫና የፕሮፌሰር መኮንን አሰፋ ሽልማት ተበርክቶላቸዋል፡፡